አዲስ አበባ ነሐሴ፣ 18/ 2015 (የፕ.ል.ሚ)
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ፍፁም አሰፋ ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት UNCIEF በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ከሆኑት ማሪኮ ካጎንሺማ ጋር የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ሴቶች እና ህጻናት ላይ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ መክረዋል።
በውይይታቸውም በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እና የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን በተመለከተ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት አስፈላጊነት ላይ ሀሳብ አንስተዋል፡፡

የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎንሺማ እንዳሉት ድርጅቱ በአየር ንብረት ለውጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ክትትልና ግምገማ፣ ትምህርት፣ ንፅህና እና የምግብ ጥበቃን ጨምሮ በርካታ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ እየሰራ ሲሆን እንደ ያላቻ ጋብቻ፣ አካል ጉዳተኝነት እና የፆታ እኩልነት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የባህሪ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ እያከናወነ ላለው ተግባር አድናቆት እንዳላቸውና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በጋራ ለመስራት ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው ተናግረዋል።በዕለቱ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በዋናነትም በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ጥናቶችን ስለማካሄድ፣ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅእኖዎች ለመቀነስ ፕሮግራሞችን ስለማዘጋጀት ፣በሴቶች እና ህፃናት ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ግንዛቤን ማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ የመንግስት እና የማህበረሰብ ተዋናዮችን አቅም ማሳደግ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ እና የUNCIEF ተወካይ በእነዚህ እና በሌሎች ውጥኖች መሻሻል ላይ ለመወያየት መደበኛ ስብሰባዎችን ለማድረግ ተስማምተዋል።
ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በዱባይ በሚካሄደው ተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ኮንፈረንስ COP28 ኢትዮጵያ ያላትን ዝግጅት በማንሳት ኢትዮጵያ በጉባኤው ለምታደርገዉ ተሳትፎ የዩኒሴፍን ድጋፍ ጠይቀዋል።
የዩኒሴፍ በኢትዮጲያ ምክትል ተወካይ ካጎንሺማ ዩኒሴፍ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ጥረት ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው ፤ ለዚሁም ጉዳይ በዘመናዊ ግብርና፣ የውሃ አያያዝ እና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ ዩኒሴፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ዩኒሴፍ የሴቶችና ህጻናትን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የመቋቋም አቅም ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ ሴቶች ልጆችን ማስተማር፣ ህፃናትን ከጥቃት መከላከል እና የፆታ እኩልነትን ማስፈን በመሳሰሉት የጋራ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ በ COP 28 የምታደርገው ተሳትፎ ስኬታማ እንዲሆንም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ እና በዩኒሴፍ መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚኖረው ትብብር አዎንታዊ እርምጃ የሚኖረው ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ተጨባጭ ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች በጋራ እንደሚሰሩ ይጠበቃል።