ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) ፎረም ኢትዮጵያ ስለምታዘጋጀው የ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ተወያየ።
===================================================================
አዲስ አበባ | ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም
ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) ፎረም እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 8-10/ 2025
በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በሚካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ (The 2nd Africa Climate Summit/ACS2) ዝግጅቶችን ለመወያየት ኢንተር-ሌክዠሪ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስብሰባ አካሄዷል። የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን፣ አፍሪካ በአየር ንብረት መፍትሄዎች ዓለም አቀፍ መሪ እንድትሆን ኢትዮጵያ ያላትን ራዕይ ለፎረሙ አባላት አስረድተዋል።
ክቡር አቶ ስዩም፣ CRGE ፎረም በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተግባራት ጉዞ ውስጥ የተጫወተውን ወሳኝ ሚና አፅንኦት ሰጥተው፣ የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካ አቀፍ የአየር ንብረት ተነሳሽነቶች አህጉር አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ጥረቶችን እንዴት ማነሳሳት እንደሚችሉ አብራርተዋል።
በስብሰባውም የመንግስት ተቋማትን፣ ኤምባሲዎችን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካላትን እና አለም አቀፍ ድርጅቶችን ያቀፈው የፎረሙ አባላት፣ ኢትዮጵያ ትርጉም ያለው 2ኛ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
የፎረሙ አባላት ለፎረሙ በአዲስ መልክ የተዘጋጁ ቁልፍ የውጤት አመልካቾችን (KPIs) እና የፎረሙ አባላት በአየር ንብረት ትግባራት ኢትዮጵያን ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ተነሳሽነት መቃኘትንም ያካተቱ ነበር።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይገር አረንጓዴ ፎረም እ.አ.አ. በ2018 የተመሠረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሰብሳቢነት እና በኖርዌይ እና በብሪቲሽ ኢምባሲዎች ምክትል ሰብሳቢነት በተባበሩት መንግስታት ፀሃፊነት እየተመራ ይገኛል።