5ኛውን ዙር የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ለማካሄድ የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዉይይት አካሄደ።
********************************************************
ሐምሌ 6/ 2016 ዓ/ም አዲስ አበባ (የፕ.ል.ሚ)
5ኛውን ዙር የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) እ.ኤ.አ በ2024/25 ለማካሄድ የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ ለሁለተኛ ጊዜ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዉይይት አካሄደ።
እንደ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የመራባት፣ የህጻናት እና የእናቶች ጤና፣ አመጋገብ፣ ንፅህና፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ የስርዓተ-ፆታ ተለዋዋጭነት፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት እና የውሃ ጥራት ባሉ ቁልፍ አመልካቾች ላይ ከፍተኛ ጥራት ያለው መረጃ ይሰጣል የተባለው የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ቢሮ አብይ ኮሚቴው ባደረገው ስብሰባ ተገልጿል።
ውይይቱም የጥናቱ ዝግጅት አሁን ያለበት ደረጃ፣ የመስክ ቁሳቁሶች እና የሰው ሃይል አቅርቦት ስለመሟላታቸው፤ ለጥናቱ የተመደበው በጀት አሁናዊ ሁኔታ በሚሉት ጉዳዮች የጥናቱ አብይና ቴክኒካል ኮሚቴዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ፍፁም አሰፋ እንደተናገሩት የጥናቱ የመስክ ስራ በሚጀመርበት ወቅት ተገናኝተን ምክክር ማድረጋችን ለጥናቱ ውጤታማ መሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰው በዝግጅቱ ወቅት ያሉትን ችግሮችና ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን በጋራ ሆኖ ለመመልከት እድል እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ክብርት ሚኒስትሯ በጥናቱ ዝግጅት ሂደት ያጋጠሙትን ችግሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ለመፍታት የተሞከረበት መንገድ ለጥናቱ ውጤታማ መሆን በሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለውን ቁርጠኝት የሚያመለከት ሲሆን ይህ ውይይት ለየት ባለ መልኩ በዝግጅት ወቅት ያጋጠመንን ቴክኒካል ችግሮች አስፈላጊ የሆኑ ቴክኒካል መፍትሔዎቻቸውን ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በዕለቱ በኢትዮጵያ እስታስቲክ አገልግሎት የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ዝግጅት ከጀመረበት ጀምሮ የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራት የቀረቡ ሲሆን ይሄም መጠይቁን ማዘጋጀትና ታአማኒነቱን የማረጋገጥ ሂደት፤ የመጣበት የዕድገት ደረጃ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተፈቱበት መንገድ እንዲሁም ወደ ተግባር ስለሚገባበት እና ወደ መሬት ስለሚወርድበት ሂደት በተጨማሪም የጥናቱ ዝግጅት በጀት አጠቃቀም ገለፃ ተደርጓል።
በመንግስት ድጋፍ፣ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ እና በልማት አጋሮች የሚካሄደው የሰነ-ሕዝብና ጤና ጥናት በቀጣዩ የነሐሴ ወር እንደሚጀመር የተነገረ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ሰማሪታ ሰዋሰው፣ የሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴር ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ምክትል ዳይሬክተር ኤሌኖር ታንፒዬንጎ እና ሌሎች የልማት ድርጅት ተወካዮች በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ኤሌኖር ታንፒዬንጎ (USAID) በበኩላቸው የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ዋና ትኩረት ለማህበረሰብ ቁልፍ በሚባለው ጤና ዘርፍ ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአተገባበሩ ላይ ያሉ ችግሮች ቀደም ተብለው መፍትሔ እንዲያገኙ አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን እና ድጋፎች ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አንስተዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሯ አያይዘውም በስራዎች ግልፅ መሆን ይገባናል፡፡ በዝግጅቱ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በአተገባበሩም ወቅት ችግሮች እንደሚኖሩ የሚገመት ስለሆነ ድርጅታችን በየትኛው ሁኔታ ለማገዝ ፍቃደኛ ስለሆነ ለኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ውጤታማነት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
በስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) ዝግጅት ያለበት ሂደት የሚያሳውየው ይሁን በሚያሰብል ደረጃ ላይ እንዳለ ነው ያሉት ሚኒስቴሯ ያሉት ችግሮች ሊስተካከሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት (EDHS) መደረጉ መረጃዎችን ከማግኘት ረገድ አሰፈላጊ መሆኑን ገልፀው ያሳየው የዕድገት ደረጃ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒሰቴር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ፣ አያይዘውም ጥናቱን ለማድረግ ከፀጥታ ችግር አኳያ የሚኖረውን ክፍተት ለመቅረፍ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን አመቺ በማድረግ መስራት እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን በቀጣይም የሚኖሩት ሂደቶችና ችግሮችን በጋራ በመወያየት አያስተካከሉ መሄድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት (EDHS) በእርግጥም በኢትዮጵያ ሁኔታ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ብቅ ያለ የአገሪቱን የስነ-ሕዝብና የጤና ተግዳሮቶች ለመረዳትና ለመፍታት ቁልፍ መሣሪያ አንደሚሆን ተነስቷል።