የኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከፌደራል የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋራ በመተባበር በተዘጋጀውና “ሙስናን መከላከል የዜግነት ግዴታዬን እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ሙስናን እና ብለሹ አሰራርን ለመከላከል የሚወስዱ ስልቶች ላይ ባተኮረው ስልጠና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ጥሩማር አባተ፤ የፌደራል የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ም/ኮሚሸነር ክቡር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራር አካላት እና ስራተኞች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና የስራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል፡፡
ስልጠናው ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒሰቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ጥሩማር አባተ ባስተላለፉት መልዕክት ሙስና የአንድን ሀገር መልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የስብአዊ መብት መከበር በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ፣ ሐቀኝነትን በማጓደል የህገ-ወጥነትን ባህሪ የሚያላብስ እና ሀገርን ሊበትን የሚችል አለማቀፋዊ ወንጅል እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ሁላችንም ከመንግስትና ከህዝብ የተሰጠንን ኃላፊነት በመወጣት ሀገራዊ የመልማት አቅማችንን ተጠቅመን በሀገራችን ዕድገት ላይ ጥላውን የሚያጠላውን ሙስና ለመከላከል የተጀማመሩ አሰራርን የማዘመን ስራዎችን ከዳር ማድረስና የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራርን እውን በማድረግ የህዝባችንን ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁላችንም የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ሚንስትር ዴኤታዋ አያይዘውም ሙስና በመንግስት አቅም ብቻ ለመከላከል አዳጋችና ችግሩ የጋራ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንዳለበት ሊታወቅና ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የሬደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ም/ኮሚሸነር ክቡር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው ሙስና የሀገር ጠንቅ ነው፤ ይህንን የአስተሳሰብና የአመለካከት ዝቅጠትን መከላከል የሚቻለው ሳንሰለች ደጋግመን በማስረፅ፣ በማስተማር እና በማስመዝገብ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና የሙስና ወንጀሎች ምንነት፤ አይነቶች እና ልዩ ባህሪያት፤ 25ቱ የሙስና ወንጀሎች ምንነት፤ በዘርፉ የሚነሱ የሙስና ጉዳዮች፤ ስጋቶች እና ተጋላጭነት እንዲሁም በዘርፉ የሚነሱ የሙስና መከላከያ ስልቶች ላይ ሰፋ ያለ ገለፃ ከኢትዮጰያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በመጡ በዶክተር ዮሐንስ ጴጥሮስ አማካኝነት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን በመድረኩም የቡድን ውይይቶች፣ ጥያቄና ማብራሪያዎች እንዲሁም የሃሳብ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡