3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት የግምገማ ምክክር መድረክ ተካሄደ።
====================================================================
አዲስ አበባ | ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም
የኤፌዲሪ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሶስተኛውን ሀገር አቀፍ የፈቃደኝነት ግምገማ (VNR) 2025 ረቂቅ ሪፓርት ዙሪያ ብሔራዊ ባለድርሻ አካላትን ያሰባሰበ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ዛሬ በሃይሌ ግራንድ ሆቴል አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የሕዝብ ተወካዬች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ የልማት ግቦቿን ከተባበሩት መንግስታት ግቦች ጋር በማስተሳሰር እየሰራች እንደሆነም አንስተው የዘላቂ ልማት አጀንዳ 2030 ተፈጻሚ እንዲሆን ውጤታማ ስራን እያከናወነችም ነው ብለዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው የሪፖርት ዝግጅቱ በርካታ ተቋማትንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መሆኑን በመጠቆም በገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ተገምግሞ መዘጋጀቱን አሳውቀዋል። በተጨማሪም ሊጠናቀቅ አምስት ዓመታት በቀሩት የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ለሀገራት እያጋራች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በምክክር መድረኩም የVNR 2025 ረቂቅ ሪፖርት አጠቃላይ ገለጻ ቀርቦ ጥልቅ ውይይት እና የጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ተካሂዷል። ከመድረኩ ጠቃሚ ግብረ መልሶች እና ልምዶች መገኘታቸውን ተጠቁሟል።
ይህ የምክክር መድረክ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ትግበራ ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነት፣ አካታች እና ግልጽነት ባለው መንገድ ሪፖርት ለማቅረብ ያላትን የማያወላውል አቋም ያሳየ ነው።