በኢትዮጵያ ምዘና ለመልካም አስተዳደርና አካታች ዘላቂ ልማትን በመሠረታዊ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አቅም መሆኑን በመገንዘብ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ጥሩ ማር አባተ ገለፁ።
============================================
አዲስ አበባ | ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም (ፕ.ል.ሚ)
ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህንን የገለፁት ዛሬ በተጠናቀቀው የአፍሪካ ምዘና ማህበር (AfrEA) 25ኛ ዓመት የ3 ቀናት አህጉራዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡
ለሶሰት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ በምዘና ዘርፍ በተሳታፊዎች መካከል የእውቀት ሽግግር፤ የልምድ ለውውጥ የተካሄደበት እና አዳዲስ ሀሳቦች እንዲመነጩ መሰረት የጣለ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ጥሩ ማር በመሰረታዊ ጉዳዮችና በፖሊሲ ደረጃ ከተነሱ ሃሳቦች በምክክሩ ምዘና ከቴክኒካል መሣሪያነቱ ባሻገር የመልካም አስተዳደርና አካታች ዘላቂ ልማትን በመሠረታዊ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አቅም ጭምር መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ለምዘና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እና ውሳኔ ሰጪነት ባህልን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን፤ ጠንካራ የክትትልና ግምገማ (M&E) ሥርዓቶች በመዘረጋት በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊነታቸውን በማመን ተግባራዊ ርምጃዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪ ሀገራዊ የምዘና ስርዓቶችን በማጠናከር፣ ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ እና የግምገማ ማዕቀፎችን ወደ ልማት ፕሮግራም እና ፖሊሲ በማዋሃድ ኢንቨስት ማድረጉን የተናገሩት ወ/ሮ ጥሩ ማር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና በመንግስት ኤጀንሲዎች ምዘናን ተቋማዊ ለማድረግ እና ከአፈጻጸም የምናገኘው ትምህርት የእድገት ጎዳናን የሚያሳውቅ እንዲሆን ጭምር በንቃት እየተሰራ ነው በማለት እብራርተዋል።
ሚኒሰትር ዴኤታዋ አክለውም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ስኬታማት የበኩሏን ድርሻ እንደምታበረክት ጠቁመው በሁለት ማዕቀፎች ሰላማዊ፣ የበለጸገች እና የተዋሃደች አፍሪካ የጋራ ምኞታችንን የምታሳካ እንድትሆን መስራት ተገቢነቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድም ቢሆን ምዘና አንዱና ወሳኝ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ በመሆኑ የሚሰራውን እና የማይሰራውን ለመለየት ከሁሉም በላይ ማንም ወደ ኋላ እንይቀር እንደሚረዳም ጭምር ገልፀዋል።