የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን በተመለከተ የሥራ አስተባባሪ ኮሚቴው የመጀመሪያ ምክክር አካሄደ።
========================================================================
አዲስ አበባ | ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (ፕ.ል.ሚ.)
በኢፌዴሪ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ለማዘጋጀት ዝግጅቶችን እየተደረጉ መሆኑን አስታውቋል። ይህንንም ተከትሎ የጉባዔው የሥራ አስተባባሪ ኮሚቴ የመጀመሪያውን የምክክር ስብሰባ መድረክ አካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ እንዲሁም አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተልዕኳቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በንቃት ለመወጣት ቁርጠኛ ናቸው ብለዋል።
ይህ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 08-10/2025 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ እንዲሁም ከሴፕቴምበር 5-7, 2025 የ3ቀን ቅድመ ጉባኤ ስብሰባ እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹ ሲሆን ለዚህ ጉባኤ መሳካት የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የልማት አጋሮችን ያካተተ ሁለንተናዊ አደራጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ጉባኤው የአፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ጥረቶችን ይበልጥ ለማሳደግ እና በአንድነት በመቆም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ወሳኝ መድረክ እንዲሆን ታስቦ እየተዘጋጀ እንደሆነና ለጉባኤው ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብርና አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑም ክቡር አቶ ስዩም ገልጸዋል።
የጉባዔው የሥራ አስተባባሪ ኮሚቴው የሚመራበት መነሻ ዕቅድም ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እ.ኤ.አ በ2023 በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ ይታወቃል።