በካርቦን ግብይት ስርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
************************************************
ግንቦት 6/ 2016 ዓ.ም፥አዲስ አበባ (የፕ.ል.ሚ)
በካርቦን ግብይት ስርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
በመድረኩ ላይ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን አስታዉቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰባት የምትገኜዉ ኢትዮጵያ የተለያዩ የመከላከል ስራዎችን ብትሰራም ችግሩ አለማቀፍ ከመሆኑ አንጻር እንደ ጎርፍ ፥ ድርቅና ሌሎች መሰል አደጋዎችን እያስተናገደች ነዉ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዲኤታዉ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን በሃያት ሪጄንሲ ሆቴል በኢትዮጵያ ካርቦን ንግድ ማዕቀፍ ዙሪያ በተካሄደዉ ምክክር ላይ ተገኝተዉ እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ አለምን እፈተነ ያለና በአሳሳቢነቱም ከፍተኛዉ ነዉ።
በተለይ ጉዳቱ ለብክለቱ እምብዛም አስተዋጽኦ በሌላቸዉ ታዳጊ ሃገራት ላይ ክፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታዉ ኢትዮጵያም የጉዳቱ ሰለባ መሆኗን አብራርተዋል። መንግስት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ያነሱት አቶ ስዩም ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ፥ የአየር ንብረት ፖሊሲና ፕላኒንግን በአግባቡ መተግበር ፥ የመላመድና ማጣጣም ስራዎችን በትኩረት መተግበር ፥ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ (NDC) ፥ የረዥም ጊዜ አነስተኛ የልቀት መጠንን እዉን ከማድረግ ጄምሮ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ በ10 ዓመቱ ሃገራዊ እቅድ አንዱ ምሰሶ እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዉ አብራርተዋል።
አረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት ስራዎችም መንግስት ያለዉን ቁርጠኝነት ያሳየባቸዉ ስራዎች መሆናቸዉን ያነሱት አቶ ስዩም የታዳሽ ሃይል ልማት ሃገሪቱ ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሃጋራትን እያሳተፈቺበት ያለ ስራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለዉጥ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት የካርቦን ንግድን መሰለ እድልም አምጥተዋል ያሉት አቶ ስዩም ተጠቃሚ የመሆን ጅምሮች ቢኖሩም በሚፈለገዉ ደረጃ ለመሳተፍ ዘርፉን በህግ በስርአትና በማእቀፍ መምራትም ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የሚረዳ የካርቦን ግብይት ማዕቀፍም በአለም ባንክ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል ። ከዚህ ሚገኜዉን ገቢ በማሳደግ ሃገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግና የአየር ንብረት ለዉጥን የመከላከሉን ስራ ዉጤታማ ለማድረግ የተጄመሩ ስራዎች ተጠናክሩ መቀጠል እንዳለባቸዉ ያነሱት አቶ ስዩም መኮንን በዚህ ረገድ የአለም ባንክ እያደረገ ያለዉን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአለም ባንክ የመሰረተልማት ፕሮግራም መሪ የሆኑት ዥያወፒንግ ዋንግ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆኑ የምትሰራዉን ስራ በማገዝ በኩል ባንኩ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል። ምክክሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና ሰፊ ዉይይትም የተደረገበት ነዉ።