በኖርዌይ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጉዳይ ላይ ስምምነት ተፈረመ፡፡
************************************************************************************************************************
የካቲት 19/2016 አዲስ አበባ (የ.ፕ.ል.ሚ)
በኖርዌይ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በአየር ንብረት ለውጥ እና የአከባቢ ጉዳይ ላይ በተሻሻው የአጋርነት መግለጫ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስምምነት ተፈረመ፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዋናነት የደን ጭፍጨፋ እና የደን መራቆትን በመግታት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን መቀነስ፤ የደን ካርቦን ክምችትን በመጠበቅ የደን ዘላቂ አስተዳደር እና የደን ካርቦን ክምችት ማሻሻል (REDD+) እንዲሁም ፡፡ በኢትዮጵያ ተለይተው በተያዙት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት መጠን ስትራቴጂ በትኩረት በመስራት የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ ዘላቂ ልማትን ማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ማስቻል ስምምነቱ የተፈራረሙባቸው ጉዳዮች ናቸዉ።
በውይይቱ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስዩም መኮንን ፣የተከበሩ አቶ አህመድ ሻዴ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የግብርና ሚኒስትር የተከበሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ፤ የአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ሚኒስትር ክቡር አንድሪያስ ኢሪክሰን እና ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮችና የUNDP ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ይሄ ስምምነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመፈረሙ ታሪካዊ ያደርገዋል ያሉት የአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለስምምነቱ ውጤታማነት ሁላችንም የራሳችንን አሻራ ልናሳርፍ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የዛሬው ስምምነት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትልቅ ዕድል አለው ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያካሄደች ያለችው ትግል ላይ ያላትን ቁርጠኝነትም ያሳየ ስምምነት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የአጋርነት ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በንግግራቸው የኢትዮጵያ እና የኖርዌይ አጋርነት ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ገልፀው ስምምነቱ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት በጎርፍ እንዲሁም ድርቅ እየተጠቃች ላለች ሀገር በጣም ትልቅ መነሳሳት እና ችግሩን ለመቀነስ የሚያግዝ እንደሚሆን ጠቅሰዋል ፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ አያይዘውም ከዚህም በፊት ከኖርዌይ መንግስት ጋር የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ፍልሰት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በአጋርነት እንደሚሰሩ ጠቅሰው የአየር ንብረት ለውጥ እና ድህነት ቅነሳ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደመሆናቸው በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያና በኖርዌይ መንግስታት መካከል የተካሄደው ስምምነት በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ወዳጅነነት የሚያጠናክር እንደሆነ አክለዋል፡፡
በኖርዌይ መንግስት በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት የኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ሚኒስትር ክቡር አንድሪያስ ኢሪክሰን በበኩላቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትዮጵያ አስጊ ደረጃ ላይ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ጥሩ ዕድል የሚከፍት ስምምነት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የኖርዌይ መንግሰት ለምግብ እና ለውሃ ደህንነት ቅድሚያ ሰቶ የሚሰራ መንግስት እንደሆነ ጠቅሰው በስምምነቱ መሰረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በማቅረብ አጋርነቱን እና ድጋፉን እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
የኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ሚኒስትር ክቡር አንድሪያስ ኢሪክሰን በመጨረሻም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ፤ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ፤ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እንዲሁም ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት መጠን ስትራቴጂ ላይ እየሰራች የምተገኘውን ስራዎችና እየተመዘገቡ የሚገኙትን ውጤቶች በበለጠ የሚያስቀጥለውን ስምምነት በመፈራረማችን ደስተኞች ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከስምምነት ፊርማው በኃላ የግብርና ሚኒስትር የተከበሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ሚኒስትር ክቡር አንድሪያስ ኢሪክሰን፤ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር አካሂደዋል፡፡