የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ ከኒዊዚላንድ አምባሳደር ሚካኤል አፕተን ጋር በጽህፈት ቤታቸዉ ተወያዩ፡፡
*******************
አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015 (የፕ.ል.ሚ)
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ ከኒዊዚላንድ አምባሳደር ሚካኤል አፕተን ጋር በጽህፈት ቤታቸዉ ተወያዩ፡፡
ዉይይታቸዉ በዋናነት በአየር ንብረት ለዉጥ መከላከልና በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ላይ ያተኮረም ነበር፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት መከላከል ስራዎች በርካታ ዉጤታማ ተግባራትን ማከናዎኗን ገልጸዋል፡፡ ለአየር ንብርት ለዉጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጄምሮ መንግስት ከሃገራቀፍ ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎች እና እቅዶች ጋር በተጣጣመ መልኩ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች መርሐ-ግብሮችን በመቅረጽ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ከጉባኤዎች እና አውደ ጥናቶች ያለፈ መልክአ ምድርን ዳግም ወደነበረበት በመመለስ እና የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።
መንግስት እ.ኤ.አ እስከ 2050 በኢትዮጵያ የካርበን ልቀት ዜሮ ለማድረስና በዓመት ከ865 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ በግንቦት/2015 ይፋ ማድረጉ የገለጹት ክብርት ሚኒስትር ይህም ሃገሪቱ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አረጋግጠዋል።
በተባበሩር አረብ ኤምሬቶች ዱባይ በሚካሄደው 28 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ክብርት ሚኒስትር አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኒዊዚላንድ አምባሳደር ሚካኤል አፕተን በበኩላቸዉ በቴክኖሎጂ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ፣ በታዳሽ ሃይል ልማት፣ በአስተዳደር ፣ በግብርና ስራዎች ከኢትዮጰያ መንግስት ጋር የጀመሯቸዉን የትብብር ተግባራት እንደሚያጠናክሩ ለክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ገልጸዉላቸዋል፡፡ በተለይም በሃገራዊ ምክከር ኮሚሽን በኩል የሰላም ስራዎችን እንደሚደግፉ አምባሳደሩ አስታዉቀዋል፡፡
የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ሁለትን ዝርዝር ይዘት ፣ ቁልፍ ትኩረቶችና ምሰሶዎች በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ሁለቱ ሃገራት ይበልጥ በኢንቨስትመንት ተባብረዉ ቢሰሩ በኢትዮጵያ መልካም እድሎች መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
ነዊዚላንድ ለኢትዮጵያ በሰዉ ሃብት ልማት በአጭርና በረዥም ጊዜ ስልጠናዎች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ አረጋግጠዋል፡፡