19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ማስተናገድ ጀምራለች።
********************************************
አዲስ አበባ ነሃሴ 8/2015 (የፕ.ል.ሚ)
19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ "የአፍሪካ የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም ትብብርን ማጎልበት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ በባለሙያዎች የተባበሩት መንግስታት ተቋሟትና የአጋር ድርጅት ኃላፊዎችም በተለያዩ አካባቢያዊ አጀንዳዎች ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው ለ28ኛው አለም አቀፍ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አህጉራዊ አቋም የሚያዝበት ይሆናል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ለተ.መ.ድ የአካባቢ ፕሮግራምና አለም አቀፍ አስገዳጅ የፕላስቲክ ህግ ላይ የአፍሪካን የጋራ አቋም ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ውይይቱን በይፋ የከፈቱት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሳንዶካን ደበበ ናቸው።
በመክፈቻ ንግግራቸው 19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ “በአፍሪካ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ፥ ዕድሎችን መጠቀም እና ትብብርን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ወቅታዊና እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል ።
አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣዉ የአየር ንብረት ለዉጥ እና የአካባቢ ብክለት ከፍተኛ ችግር ዉስጥ እየገባች መሆኑን ያብራሩት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታዉ ይህ ስብሰባ በችግሮቻችንና በመፍትሄዎቹ ላይ ለመወያየት ተጨባት የጋራ ለውጥ ለማምጣት እንደ መድረክ ያገለግላል ብለዋል።

የአፍሪካ መንግሥታት፣ ተቋማትና የልማት አጋሮች ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ሳንዶካን ደበበ አፍሪካ አዳዲስ መፍትሄዎችን የሚጠይቁ ልዩ ልዩ የአካባቢ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟት አብራርተዋል። በንግግራቸዉ የአረንጓዴ አሻራን፥ የስንዴ ምርትና ምረታማነትንና ሌሎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተሰሩ ስራዎችን ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታዉ አቶ ሳንዶካን ደበበ ዛሬ ከተጀመረዉ የኤክስፐርቶች መድረክም ይሁን ከዋናዉ የሚኒስትሮች ጉባኤ መፍትሄን የሚያፈልቁ ቁልፍ ዉሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ እስከ አርብ ድረስ የሚካሄድ ሲሆን ከ47 በላይ የአፍሪካ ሀገራት በመድረኩ እንደሚወከሉ እና ከ400 በላይ የተለያዩ የአፍሪካ አገራትና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡